የአባታችን የእስትንፋሰ ክርስቶስ የተወለዱበት ቦታ ዳውንት ፀውን ዓባይ ይባላል:: በሰሜን በኩል የእናታቸው ሃገር ደብረ ድባ የቄርሎስ ቦታ ይባላል:: የአባታቸውም ሃገር የእግዚአብሄር አብ ደብር አጠገብ ዳውንት(ደብረአስጋጅ)ይባላል:የአባታቸውምስም መልዓከ ምክሩ ሲባሉ እናታቸው ደግሞ ወለተ ማርያም ይባላሉ:: እነዚህ ባል እና ሚስት በህግ ጸንተው የሚኖሩ እንደ ዘካሪያስ እና እንደ ኤልሳቤጥ መልካም ስራን በመስራት እግዚአብሄርን የሚያገለግሉ ነበሩ:ቀድመውም 2 ልጆችን ወልደው ነበር እና ከዛም እመቤታችንን የተባረከ እግዚአብሄርን የሚያገለግል በጸሎቱ ሰውን የሚጠቅም ልጅ እንድትሰጣቸው ዘወትር ይለምኗት ነበር:: እግዚአብሄርም ፀሎታቸውን ሰምቶ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሚያዚያ 8 ተፀነሱ: ታህሳስ 8 ቀን ተወለዱ:: ልክ በተወለዱ እለትም ተነስተው በግራቸው ቆመው 3 ጊዜ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስቅዱስ ብለው አመሰገኑ:: 9 ጊዜም ሰገዱ:: ከዚህም በኋላ በ40 ቀናቸው ጥምቀትን ተጠምቀው ስማቸውም እስትንፋሰ ክርስቶስ ተባለ:: ከዚያም ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸው አደጉና አባትየው ዋሻ ውስጥ 60 አመት ወደ ኖረ ቅዱስ ኪራኮስ ወደ ሚባል አባት
ወሰደው ትምህርት እንዲያስተምረው ለመኑት:: ከዚያም ፃድቁ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ በአባ ኪራኮስ ተመርቆ ትምህርቱን ጀመረና እንደሌላው ሰው ጊዜ አልፈጀበትም:ወዲያው ይረዳ ነበር:: ጻድቁ አባታችን የተለያዩ የሃይማኖት ትምህርቶችን በፍጥነት ተማረ:: በክርስቶስ ፍቅር በእመቤታችን ፍቅር ልቡ ደማ:: በውስጥ በአፍአ ድንግል ስትሆን የህያው የእግዚአብሄር አብ የባህርይ ልጅ ወልድን በጡቶቿ ወተት አጥብታ ያሳደገችው በሁለት ወገን ድንግል የምትሆን መልካሚቷ እርግብ እመቤታችን ጽጌ የሚባል ልጇን እንደምትስም እንዲሁ ጻድቁ አባታችንን ትስመው ነበር:: አባታችን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ቅኑት እንደገበሬ ፅሙድ እንደበሬ ሆኖ ሳይመነኩስ የምንኩስናን ስራ መስራት ጀመረ:: እንደ እሳት ወላፈን ፈጥኖ የሚያልፍ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ህሊናው እንደ እሳት ነደደ:: አንደበቱም 46ቱን ብሉያትን 35ቱን ሃዲሳትን መጽሃፍ አንባቢ አደረገው:: ከዚህም ሌላ ቅዱሳት መጽሃፍትን:-150ውን መዝሙረ ዳዊት: ድርሳናትን: ውዳሴ ማርያምን: የጻድቃን እና የሰማእታትን መልክአ: አስራ ስምንቱን ተአምረ ማርያም:ተአምረ እየሱስ: የሰኔ ጎሎጎታ: ልፋፈ ጽድቅ: እቀበኒ ክርስቶስ: 7ቱ ኪዳናትን: ባርቶስ እና ገድለ አቡነ ኪሮስ: ጊዮርጊ: ኤዎስጣቴዎስ: ገብረ መንፈስቅዱስ: ተሰአቱ ቅዱሳን እንዲሁም ሰይፈ ስላሴን እና ሰይፈ መለኮትን እንዲሁም ሌሎችን ቅዱሳን መጽሐፍቶችን ዘወትር አብዝቶ ይፀልይ ነበር:: ጻድቁ አባታችን ጾምና ጸሎትን ትዕግስት አርምሞ ልጉአም ሆኑለት:: እግሮቹ በሐዋርያት ወንጌል ጭንጫ ላይ ቆሙ:: ቅድስት ንጽህት ድንግል በምትሆን በእመቤታችን በማርያም ፍቅር ገመድ ተጎተተ:: የአሸናፊ የእግዚአብሄር ስሙን በመፍራት ሰውነቱን ይገስጻል:: በጻድቃን እና በሰማእታት ጎዳና ሰውነቱን ያሮጠዋል:: ከዚህም በኋላ አባ ኪራኮስ አባታችንን መርቆ ወደ አባቱ ሰደደው:: ከዚያም አባትየው ስሙ ማርቆስ ወደሚባል ጳጳስ ክህነት ይሰጠው ዘንድ ወሰደው:: ጳጳሱም ባርኮ ዲቁና ሾመው እና ወደ ሃገራቸው ዳውንት ተመለሱ:: በእመቤታችን እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በድቁና ያገለግል ጀመር:: አባቱን እና እናቱንም በማገልገል እስከ 14 አመቱ ድረስ ተቀመጠ በኋላም በ 14 አመቱ አለምን ንቆ ይመንን ዘንድ ለቤተሰቦቹ ነገራቸው አባቱም ቤተ ክርስቲያን ሄዶ አልቅሶ ቢጸልይ "ይመነኩስ ዘንድ ይሂድ ስልጣኑ እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ይላል ስም አጠራሩ እስከ አለም ዳርቻ ይደርሳል"የሚል ቃል ከሰማይ ሰማና በፍቅርና በሰላም አሰናበቱት:: አባታችን በ14 አመቱ ብዙ ገዳማትን እየጎበኘ ወደ ደብረ ሃይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞአ ደረሰ:: ከዚያም እንደገዳም ስርዓት 3 ዓመት ተፈተነና ምንኩስናን ለበሰ:: ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ድቁና ወደ ሾመው ጳጳስ ሄዶ ቅስናን ተቀበለ:: ከጥቂት ቀንም በኋላ ቁምስናን እና ኤጲስቆጶስነትንም ሾመው:: አባታችን "ጌታችን ሰውነቱን በገራህተ መስቀል የጣለ ነፍሱን ያገኛታል:: ስለኔ ሰውነቱን በገራህተ መስቀል ይጣል"ያለውን አስቦ በጾም በጸሎት በትርህምት በስግደት ኖረ:: እንደ 12ቱ ሃዋርያት አጋንንትን እያወጣ: ድውያንን ይፈውስ ለምጻምን ያነጻ ጀመር:: የአባታችን ተአምር በምድረ ኢትዮጵያ ተሰማ ህዝቡም እሱን ያይ ዘንድ ካለበት ይመጣል:: ከዚያም አባታችን ኢትዮጵያን እየተዘዋወረ ያስተምር ይጸልይ ጀመር በኋላም በ33 አመቱ ወደ ደብረ ድባ መጥቶ ሚያዚያ 9 ቀን ምንኩስናን ተቀበለ:: በዚያች ቀንም አስኬማን: ቅናትን: ቀሚስን: መታጠቂያን: መስቀልን: በትርን: ጭራንና ስእልን ተቀብሎ ሲጸልይ ዋለ:: ከዚያም እንዳስለመደው በየሃገሩ እየተዘዋወረ እያስተማረና ድውይን እየፈወሰ ሃገሪቷን አቀና በየጊዜውም የሚነሱ ንጉሶች ይመጡና ከአባታችን ዘንድ ይባረኩ ነበር:ብዙ ልጆችም አፍርቶ ነበር በስተመጨረሻም ጌታችን ከእናቱ እና ከብዙ ቅዱሳን ጋር ሆኖ ወደ አባታችን መጥቶብዙ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: በስተመጨረሻም አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ በሚያዚያ 9 ቀን አርፉ:: የአባታችን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ረድኤት እና በረከት አይለየን አሜን!!!!!
ምንጭ ገድለ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
0 comments:
Post a Comment